Ethiopia: ንግድ ባንክ ንፉግ ሆኗል በሚል የቀሰቀሰው ተቃውሞና በሳምንቱ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕስ የነበሩ ጉዳዮች
በሳምንቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተፈናቃዮች ንፉግ ሆኗል በሚል የተቀሰቀሰ ሙግት፤ የሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ መራዘም እና ሐሰተኛ ዜና እና የኢትዮጵያ ኹናቴ ያሳሰባቸው የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መልዕክት ትኩረት ያገኙ የማኅበራዊ ድረ-ገፆች መወያያ ነበሩ። ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በአማራ ክልል ለተጠለሉ ዜጎች እርዳታ ለማሰባሰብ በተካሔደው መርሐ-ግብር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ንፉግ ሆኗል በሚል የቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ ትችት እና ውዝግብ በሳምንቱ አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል። አያሌው መንበር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "የአማራ ተፈናቃዮችን ቴሌቶን በሚመለከት አንዳንድ ቅሬታዎችና መጣራት ያለባቸው ጉዳዮች" ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ይኸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጉዳይ ይገኝበታል።
አያሌው "የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተፈናቀሉ አማራዎች በተደረገው ቴሌቶን ምንም አይነት ድጋፍ አለማድረጋቸው የሚነግረን ነገር እንዳለ አልዘነጋነውም" ሲሉ በግል የፌስቡክ ገፃቸው ሐሳባቸውን አስፍረዋል። ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው "ንግድ ባንክ ሀብታሙን እንጅ ድሃውን አማራ አልፈልገውም በማለቱ በርካቶች አማራጭ ባንክ እየፈለጉ ነው። ሀብት ያለው አማራም ከድሃው ወገኑ ጎን መቆሙን አሳይቷል። ገንዘቡን ከንግድ ባንክ በማውጣት ደግሞ ይበልጥ አጋርነቱን ማሳየት አለበት" ሲል በንግድ ባንክ ላይ የተነሳውን ተቃውሞ አበረታቷል። ጌታቸው በተቃውሞ የተቀዳደዱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መገልገያ ደብተሮች የሚያሳይ ምስል በፌስቡክ ገጹ አሰራጭቷል።